የመጽሐፉ ዓላማ
ዓላማው፡- የከበረ፤ ጤናማና ውጤታማ ተግባቦት ወይም ኮሚዩኒኬሽን ምን እንደሚመስልና እንዴት መሆን እንዳለበት ከወጣቱ ትውልድ ጋር በመወያየት ለመማማር የታሰበ መጽሐፍ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ስለ ኮሚዩኒኬሽን ምንነትና ውጤት የላቀ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በዚህ ርዕስ ላይ በጥልቀት በመወያየትና በመማመር መልካም መረዳትን እንዲያካብቱ በዚሁም ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለቤተክርስቲያናቸው፣ ለኅብረተሰብ፣ ለአገራቸው መልካም አርአያ በመሆን ትክክለኛ ተግባቦት ወደ ሚያደርሰው ክብርና እረፍት ለማድረስና ሌሎችንም ለማድረስ የመፍትሄ ትውልድ እንዲሆኑ መሟገት የመጽሐፏ ዓላማ ነው፡፡
ያልተገሩና ያልተገቱ አንደበቶች፡ ባለማወቅ የሚዘሩ፤ የጨለማው ዓለም የሚያሰራጯቸው ጨለምተኛ ንግግሮች፤ ኃላፊነት የጎደላቸው መረጃዎች፤ የስድብና የመለያየት መወጋገር መወነጃጀል መናናቅ ሃሳብ ለሃሳብ አለመግባባት የቋንቋ መደበላለቅ፤ አለመደማመጥ በብዙ አቅጣጫ ቤተሰብን፤ ጓደኛን፤ ቤተክርስቲያንን፤ ኅብረተሰብን አልፎም አገር ዓለምን ከመቼውም ጊዜ እያናወጡ እንደሆነ አልሰማሁም ወይም አላየሁምና አላምንም የሚል ሊኖር አይችልም፡፡
ስለዚህ ወጣቱ ትውልድ አንደበት እሳት ነው ተብሎ በእግዚአብሔር ቃል የተጠቀሰውን በጥልቀት እየተወያዩ መልካሙንና የከበረውን የተግባቦት ስልትና ሥርዓት በዘመናቸው ለራሳቸውና ለትውልዳቸው መዘርጋትና ማስተጋባት እንዲችሉ ለማበረታታት ነው፡፡